ኢትዮጵያ ወደ ፍፁም ህብረት ! Towards a Perfect Union!

 

   በኢትዮጵያ  ጣምራ  ፌደራሊዝም  ተቋም   የተዘጋጀ  ቅርፀ  መንግሥት

የሽግግር  ፍኖተ ካርታ

ቅርጸ መንግስት

            Ethiopian Dual Federalism Government structure     2012 ዓመተ ምህረት  U.S. A

 

መግቢ

የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሁለት ጽንፎች የተወጠረ ነው። በአንድ በኩል ዘውግ ተኮር የሆነ ወይም ማንነትን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ጨዋታና የፌደራል ስርዓት ያለ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የፌደራል ስርዓቱ ከማንነት እንዲላቀቅና የፖለቲካው ስብስብ በሃሳብ ላይ ብቻ እንዲሆን የሚታገል አለ። እነዚህ ሁለት ጽንፎች የፈጠሩት አለመግባባት ሃገራችን የተሻለ መድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዳትገነባና የረጋ ሰላም እንዳይኖራት አድርገውብናል። በሁለቱ ጽንፎች መካከል ያለው ውጥረት ለጋራው በጎነታችን (common good ለምንለው ግባችን) በጋራ እንዳንሰራ አድርጎናል። ኢትዮጵያውያን በታሪካችን የመንግስት ምስረታችን (state building) የተሳካ ቢሆንም፣ በነጻነታችን የምንኮራ ብንሆንም ፣ ብዝ ሃነትን በማስተናገድ በኩል (nation building ላይ)  የሚገባንን አልሰራንም። የኔሽን ቢዩልዲንግ ስራችን ተገቢውን መስመር ባለመያዙ የነጻና የኩሩ ሃገር ሰው ብንሆንም የውስጥ የማንነት ኣያያዛችን በብዙ ችግር የተጠመደ በመሆኑ ወደፊት እንዳንራመድ እየጠለፈ ሲያሰናክለን እናያለን። በተለይ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ደግሞ የማንነት ጥያቄ  እጅግ ደምቆ ማህበራችንን እያናጋብን ነው። ስለሆነም እኛ ኢትዮጵያውያን  ኣንድ ሊያግባባን የሚችል የፖለቲካ መስመርና የፌደራል ስርዓት ልንገነባ ይገባል። ይህ ስርዓት በተለይም የሚጋጩትንና እኔበልጥ… እኔበልጥ…. ፍክክር የገቡትን ብሄራዊ ማንነትንና የብሄር ማንነትን አቻችሎ የሚያኖር መሆን አለበት። በዚህ መሰረት የኢትዮጵያን የፌደራል ስርዓት ህጸጾች በመገምገም፣ ከብሄር ተኮር ፖለቲካችንና ከዜግነት ተኮር ፖለቲካችን መሃል ያሉትን እውነቶች ለይተንና አገጣጥመን  አንድ ኢትዮጵያዊ የሆነ የፌደራል ስርዓት መፍጠር ተችሏል። ይህ የፌደራል ስርዓት የኢትዮጵያ ጥምር ፌደራሊዝም ይባላል። መቼም ሃገሮች በኩረጃ ችግራቸውን ኣልፈቱም። ሁሉም ሃገር ራሱን የሚመስል ለራሱ የሚበጅ ኣስተዳደር ይዘረጋል። እኛ የጥምር ፌደራሊዝም ተቋም አባላት ለሃገራችን ኢትዮጵያ የሚሆንና በልኳ የተሰፋ የፌደራል ስርዓት በማግኘታችን ደስታችን ወደር የለውም።ይህ የጥምር ፌደራል ስርዓት በአንድ በኩል ፍጹምነት የጎደለውን ህብረታችንን ወደ ፍጹም ህብረት የሚያሻግር ሲሆን በሌላ በኩል ግን በምንፈጥረው ፍጹም ህብረት ውስጥ የሚኖሩትን ማንነቶች ህልውና ዘወትር ሲጠብቅ የሚኖር የፌደራል ስርዓት ነው። ትልቁ የዚህ የጥምር ፌደራል ስርዓት ትሩፋት ብሄራዊ ማንነትን ከብሄር ማንነት ጋር አጣምሮ መሄድ መቻሉ ነው። አንዱ ማንነት አንዱን ሳያጠፋው ማንነቶች ተጠባብቀው የሚኖሩበት የፌደራል ስርዓት በመሆኑ ለሃገራችን ኢትዮጵያ ሽግግር ግሩም የሆነ ፍኖተ ካርታ ነው።  በተለያየ ጎራ ያሉ የኢትዮጵያ ለሂቃንም በዚህ ኢትዮጵያዊ በሆነ የፌደራል ስርዓት ተመስጠው ይገባቡበታል ብለን ተስፋ ሰንቀናል። ይህ ዶክመንት ስለዚህ ስለጥምር የፌደራል ስርዓት መጠነኛ መግለጫ የሚሰጥ ሲሆን  እኛ የ IEDF አባላት ይህንን የጥምር ፌደራል ስርዓት ሃሳብ አንግበን ኢትዮጵያ ወደ ፍጹም ህብረት እንድትገባ ንቅናቄ ጀምረናል። “ወደ ፍጹም ህብረት!” የሚለው ንቅናቄያችን ህብረታችንን የሚያድስና የኢትዮጵያን ትንሳኤ የያዘ ጥሪ ነው። ይህንን ንቅናቄ ከግቡ ለማድረስ በእውቀት፣ በገንዘብ፣ በተለያየ መንገድ ልታግዙን የምትፈልጉ ኢትዮጵያውያን በአድራሻችን እንድታገኙን እንጠይቃለን። 

 ለመሆኑ የኢትዮጵያ ጣምራፌ ደራሊዝም ተቋም ምንድን ነው?

ስያሜ

ስያሜው የኢትዮጵያ ጣምራ ፌደራሊዝም ተቋም ( IEDF Institute Ethiopian Dual Federalism) ነው።

ምን ዓይነት ድርጅት ነው?

 1. የኢትዮጵያ ጣምራ ፌደራሊዝም ተቋም  አዲስ ሃገር በቀል  የመንግስት አወቃቀር ዘዴ (Homegrown Government structure)  ያስተዋወቀ ድርጅት ነው። ይህ አዲስ የሃገር አስተዳደር ቅርጽ ለሃገረ መንግስት ግንባታና ለሽግግር ኣማራጭ  ፍኖተ ካርታ  ነው።። ብሄራዊ መግባባትን ለማምጣት አማራጭ አግባቢ ሃሳብ ያለው ተቋም ነው።

 2. የኢትዮጵያ ጣምራ ፌደራሊዝም ተቋም ኢትዮጵያ በፌደራል ስርዓቷ አካባቢ ያሉ ልዩነቶችን አስታርቃ የተሻለና ብዝሃነትን ለማስተናገድ የሚረዳ ጥምር የፌደራል ስርዓት እንድትገነባ የሚመክር የሲቪክ ተቋም ነው::

የኢትዮጵያ ጣምራ ፌደራሊዝም ተቋም አዲስ የሃገር ኣስተዳደር ቅርጽ ምን ይመስላል?

ጣምራ ፌደራሊዝም ተቋም  የፌደራል ስርዓቱን በሁለት ስቴቶች ይከፍላል። አንደኛው የፌደራል ስርዓት የብሄር ባህላዊ ፈዴራል ስቴት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የዜጎች ፌደራል ስቴት ነው። እነዚህ የፌደራል ስቴቶች በጋራው ቃል ኪዳን ላይ ተጣምረው በራሳቸው ምህዋር ላይ እየዞሩ ለጋራው በጎነታችን (common good) እንዲሰሩ የሚያደርግ የፌደራል ስርዓት ነው ጣምራ ፌደራሊዝም  ማለት። በህገ መንግስት ስራቸውን ተከፋፍለው የሚሰሩበት ስርዓት ማለት ነው:: በመሆኑም ጥምር የፌደራል ስርዓት ማለት ሃገራችን ኢትዮጵያ  ለብሄራዊ ማንነትና ለብሄር ማንነት የሚሆኑ ጎጆዎችን ሰርታ የምታኖርበት ቤት ማለት ነው። ኢትዮጵያ ሃገራችን የፌደራል ስርዓት ሳይንስን ኢትዮጵያዊ ኣድርጋና በልኳ ሰፍታ የምትተዳደርበት የመንግስት ስርዓት ማለት ነው ጥምር ፌደራል ስርዓት ማለት።

የ IEDF ምሰሶዎች ምንምን ናቸው? What are the pillars of IEDF?

የ IEDF ምሰሶዎች 4 ናቸውእነዚህም:-

 

     1. ሃገራዊ ኪዳን   Covenant

 

      2.  ሄራ    Constitution

 

      3.  የጣምራ  ፌደራል ስርዓት   Dual Federalism

 

      4. ተግባቦትና ቋንቋዎች      Communications and languages

             

 

 

እነዚህን 4 የ IEDF ምሰሶዎች እንተንትን:-

 

1.  ሃገራዊ ቃል ኪዳን ምንድንነው? What does Ethiopian Covenant mean?

 

ሃገራዊ ቃል ኪዳን የምንለው ህገ-መንግስት የምንለው ዶክመንት ኣይደለም። ሃገራዊ ቃል ኪዳን የምንለው ዶክመንት በህገ-መንግስት የማይገለጹ ነገር ግን ለማህበረሰብ ትስስር እጅግ ኣስፈላጊ የሆኑ ኤለመንቶችን የሚይዝ የቃል ኪዳን ሰነድ ነው። ይህ ሰነድ በኢትዮጵያውያን ቃለ መሃላ የሚጸድቅ ሆኖ የሃገሪቱ የመጨረሻው ከፍተኛ ሰነድ ሆኖ ሳይነካ ይኖራል። ዘመን የማይሽረው ዶግማዊ ሰነድ ሆኖ ለትውልድ ይተላለፋል።

 • ለመሆኑ ይህ ዶክመንት ይዘቶቹ ምንምን ናቸው?

ሃገራዊ የኢትዮጵያውያን ቃልኪዳን የሚከተሉትን መሃላዎች ይይዛል

   1. እኛ ኢትዮጵያውያን ያለንን የተፈጥሮ ሃብት ክህሎትና እውቀት ሁሉ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ሰውተናል:: የእኔ የእኔ የምንለው የውስጥ የቡድን ድንበር የለም። ኢትዮጵያ የእኛ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ናት።

   2. እኛ ኢትዮጵያውያን የማትከፋፈል የተባበረች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማሳለፍ ቃል ገብተናል:: እኛ ኢትዮጵያውያን ከእግዚኣብሄር በታች የማንከፋፈል አንድ ህዝብ ነን።

   3. እኛ ኢትዮጵያውያን ብዝሃነታችንን እንንከባከባለን እናከብራለን:: ትውልዶች ባህላዊ ተቋሞቻችንን እናከብራልን፣ እንጠብቃለን። እርስ በርስ እንከባበራለን።

   4. ፍቅርን ዘወትር ከፍ አድርገን እንኖራለን።

   5. እኛ ኢትዮጵያውያን ከዓለም ህዝቦች ከአለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በምንገባው            ኪዳን መሰረት ለዓለም ሰላምና ልማት በጽናት እንታገላለን።

   6. እኛ ኢትዮጵያውያን ለተባበረችው ኢትዮጵያ ልማትና ሰላም ዘወትር ሳንታክት ለመስራት ቃል ገብተናል::

   7. ሰማያችንንና ከሰማያችን በታች ከምድር በላይና በታች ያሉትን ህያዋንና ግኡዛን ፍጥረታት ሁሉ እንጠብቃለን እንንከባከባለን።

   8. እኛ ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ ለመረዳዳት ቃል ገብተናል:: ትውልድ ኣልፎ ትውልድ ሲተካ ቅርስ እየተውን የሚቀጥለው ትውልድ የተሻለ ህይወት እንዲያይ ለማድረግ እንሰራለን። ያሉንን የተፈጥሮ ሃብቶች በትውልዶች መካከል ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንጠቀማለን።

   9. እኛ ኢትዮጵያውያን ለነጻነት ለፍትህ ለህግ የበላይነት ዘወትር እንተጋለን። ዘብ እንቆማለን::

   10. እኛ ኢትዮጵያውያን በህግ በምንወስነው የጊዜ ገደብ ተወካዮቻችንን እየመረጥን መንግስት እየመሰረትን ለመኖር ቃል ገብተናል። እኛ የህዝብ ተወካዮች የመረጠንን ህዝብ በታማኝነትና በትጋት ለማገልገል ቃል ገብተናል።

   11. እኛ ኢትዮጵያውያን ለተገፉ መጠጊያ እንሆናቸዋለን። እንግዶችን በፍቅርና በደስታ እንቀበላለን። ጽንፈኝነትን ሽብርተኝነትን እንዋጋለን:: ለደካሞች ለተጨቆኑ ሁሉ እንቆማለን።

   12. እኛ ኢትዮጵያውያን ይህንን ቃል ኪዳናችንን ለመጠበቅ ዘወትር ዘብ እንቆማለን። አምላካችን እግዚአብሄር ሃገራችንን ኢትዮጵያን ይባርክ።

1.2.2. ሃገራዊ ኪዳን የምንለው ዶክመንት ከህገ-መንግስት በምን ይለያል?

 1. በይዘቱ

ሃገራዊ ኪዳን የምንለው ዶክመንት ከህገ መንግስታችን የሚለይበት ኣንዱ ጉዳይ በይዘቱ ነው። ህገ መንግስት የአንድ ፖለቲካዊ ኮሙዩኒቲ ከፍተኛ ቃል ኪዳን ሰነድ ነው ይባላል። ይህ ሰነድ አብሮነትን የሚያሳልጥ የመውጫና መግቢያ ህጎቻችን መሰረት ነው። ይሁን እንጂ አንድ ማህበረሰብ የሚተሳሰርባቸውን ዋና ዋና መርሆዎች በምልዓት ብዙ ጊዜ ኣይገልጽም። ለማህበረሰብ ትስስር የሚሆኑ እጅግ ኣስፈላጊ የሆኑ ረቂቅ ኤለምንቶችን ሲገልጻቸው አይታይም። ለአብሮነት ለአንድነት ለብዝሃነት የሚያስፈልጉ እነዚህ መርሆዎች በምልዓት ይገለጹ ዘንድ ነው ይህ የቃል ኪዳን ሰነድ የሚያስፈልገው። ለምሳሌ ያህል መረዳዳት፣ ፍቅር፣ መከባበር የመሳሰሉት እጅግ ኣስፈላጊ የመተሳሰሪያ መርሆዎች በህገ መንግስት በምልዓት ኣይገለጹም። ህገ መንግስት በአብዛኛው በአድርግ ኣታድርግ ላይ የተመሰረተ ህግ ሲሆን የሰውን ልጅ ህግ ብቻ ሳይሆን ቃል ኪዳንም ያስተሳስሩታል። በመሆኑም ይህ ሃገራዊ ኪዳን ህገ መንግስት ያልገለጻቸውን መተሳሰሪያ መርሆዎች በመግለጽ የማህበረሰቡን የአብሮነት ቃል ኪዳን ምሉእ ለማድረግ የታሰበ ሰነድ ነው።

 1. ዶግማዊ ተፈጥሮው

ኢትዮጵያውያን ሁለት የቃል ኪዳን ሰነዶች የሚኖሯቸው ሲሆን አንዱ ሄ ራ የምንለው ቀጥሎ የምናነሳው ኣሳብ ሲሆን ሌላኛው አሁን የምንወያይበት የሃገራዊ ኪዳኑ ነው። ሃገራዊ ኪዳኑ ከሄራ የሚለይበት ሌላው ተፈጥሮው ደግሞ ይህ ዶክመንት ዶግማዊ ተፈጥሮ ያለው መሆኑ ነው። በዚህ ዶክመንት ላይ የሚገለጹት መተሳሰሪያዎች ዘመን ተሻጋሪዎች የማይለወጡ ናቸው። ኢትዮጵያን ፍጹም የማትከፋፈል ማህበር ለማድረግ የሚያስችለን ኣንዱ ዶክመንት ይሄ ይሆናል። ህገ መንግስት ከቴክኖሎጂው ከእድገት ጋር እየታየ ሊሻሻል ይችላል። ሄራው ግን ለትውልድ የሚሰጥ ዶግማዊ ኪዳን ይሆናል።

 1. በአገላለጹ

ሃገራዊ ኪዳኑ ከሄራችን የሚለይበት ሌላኛው መንገድ ደግሞ በአገላለጹ ነው። ሄራችን በመሃላ በቃል ኪዳን መልክ የሚጻፍና የሚገለጽ ነው። መሃላዎቻችን በጥቂት በተመረጡ ቃላት ተገልጸው የሚጻፉ ሲሆን ለእያንዳንዳቸው እምቅ የመሃላ ቃላት ማብራሪያ የሚሰጥ ልዩ ሰነድ ይዘጋጃል።

 

1.3. የሃገራዊ ኪዳኑ ፋይዳዎች ምንምን ናቸው?

     1. ማህበራችንን ፍጹምና ምሉእ ለማድረግ

     2. ብሄራዊ ኣንድነታችንን ለማጠናከር

     3.   ሲቪክ ማህበራትን ለማጠናከር

 

1.4 በዓለም ላይ እንዲህ ዓይነት ሰነድ አለ ወይ? የዓለም ተመክሮ ምን ይመስላል?

በዓለም ላይ እንዲህ ዓይነት ዶክመንት በግልጽ ሰፍሮ እስካሁን አላየንም። ነገር ግን ሃገሮች በህገ መንግስታቸው ፕሪአምብል ላይ ኣንዳንድ የሚነካኩዋቸው ሃረጎች ኣሉ። ነገር ግን በግልጽና በምልዓት አናይም። የቃል ኪዳን ህዝብ የሚባሉት ኣይሁዳውያን የአብርሃምን ተስፋዎች ይዘው በዚህ ቃል ኪዳን ላይ እንደሚሰባሰቡ ይታወቃል። ሌሎች ሃገሮች ደግሞ ብሄራዊ መዝሙራቸው    ላይ ሃገራቸውን መውደዳቸውን ይገልጻሉ። አሜሪካ ዜግነት ስትሰጥ ከእግዚኣብሄር በታች የማንከፋፈል ኣንድ ህዝብ ነን እያሉ ዜጎች ቃል እንዲገቡ ታደርጋለች። ራሱን የቻለና የተደራጀ የሃገር ቃል ኪዳን ግን እስካሁን ኣላገኘንም። ኢትዮጵያ ይህንን ቃል ኪዳን ከገባች ለዓለም ሃገራት ትልቅ ትምህርት ለመንግስት ስርዓት አስተዋጾ ታደርጋለች።

 

2 ሄራ  Basic law or constitution

ሄራ የሚለው ቃል የኦሮምኛ ቃል ሲሆን constitution ለሚለው ቃል የበለጠ ገላጭ ቃል ሆኖ ኣግኝተነዋል። ህገ መንግስት የሚለው ቃል የሚለውን ቃል በምልዓት ኣይገልጸውምና ነው ሄራ የሚል ስያሜ የሰጠነው።

በIEDF ውቅር መሰረት ሄራ የሃገራች ሁለተኛው ከፍተኛ የቃል ኪዳን ሰነዳችን ነው። ይህ ሰነድ የህጎቻችን ሁሉ መሰረት ሲሆን መሰረታዊ ህግ ነው ። በ IEDF ውቅር መሰረት ይህ ሰነድ ሊቀረጽ የሚገባው በሚከተሉት መርሆዎች ላይ ተመርኩዞ ነው

1.  ኢትዮጵያን እንደ አንድ የማትከፋፈል የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብነት ወይም  ኔሽንነት የሚገልጽ ዶክመንት መሆን ይኖርበታል

2.  ለኢትዮጵያዊያን ዶግማዊ ኪዳን ክብርና ልእልና ይሰጣል። ይህንን ለመጠበቅ ዘብ ይቆማል።

3.  የብሄር ፌደራል ስርዓቱንና የዜጎች ፌደራል ስርዓቱን የሃላፊነት ልክ ይገለጻል

4.  በስቴትና በፌደራል መንግስት መካከል ያለውን ግንኙነት ይገለጻል

5.  የፌደራል መንግስትና ስቴቶች የሚጋሯቸውን ስልጣናት ይገልጻል።

6.   የባህል ፌደራል ስቴቶችና የአርበኞች ቤት የሚኖራቸውን ሃላፊነቶች ይገልጻል

7.   የባጀት ፌደራሊዝሙን የሚመለከቱ መሰረታዊ ጉዳዮችን ያስቀምጣል

8.  መሰረታዊ የዜጎች መብቶችን ያስከብራል

9.   መሬት ለአራሹ ይሰጣል

10. ሶስቱ የመንግስት ኣካላትን በቼክና ባላንስ ያዋቅራል

11. ዴሞክራሲያዊ ሃሳቦችን የያዘ ዶክመንት ይሆናል

12. የሱፕሪመሲ ክላውዝ (supremacy clause) ለፌደራል መንግስት ይሰጣል

 

   3. የጣምራ ፌደራል ስርዓት Dual Federalism

 

                                     የሁለቱ ስቴቶች አፈጣጠር እና ቅርጸ መንግስት

 

                   1.የብሄር ባህላዊ ፌደራል ስቴት

                   2.የዜጎች ፌደራል ስቴትc law (Constitution)

 

የብሄር ባህላዊ ፌደራል ስቴት

 

የብሄር ባህላዊ ፌደራል ስቴቶች የሚፈጠሩት ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ባህላዊ ቡድኖች ልክ ነው። እነዚህ ቡድኖች እንደ ባህላቸው ተወካዮቻቸውን ልከው አንድ የጋራ የባህል አርበኞች ቤት ይፈጥራሉ። ይህ ቤት ወደታች በየብሄሩ መዋቅር ዘርግቶ የማንነት መገለጫ የሆኑትን ባህሎች ወግ ልማዶች ይጠብቃል፣ የሰላምና የእርቅ ስራ ይሰራል። የሚመሰርታቸው ስቴቶች ግን በመሬት ላይ የሚነበብ ካርታ ኣይኖራቸውም። ባህልተኞች ባሉበት ሁሉ የዚህ ስቴት ኣባል እየሆኑ ባህላቸውን የሚካድሙበት ስቴት ነው።

የአርበኞቹ ቤት እንዴት ይመሰረታል?

የአርበኞች ቤት ተወካዮች እንደየ ባህሉ ተወካይ የሚመረጥበት ቤት ነው። ይህ ቤት ሲመሰረት ከየቡድኑ የመጡትን የባህል ተወካዮች ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ እንደ ሃገር የነበራትን ዘውድም ባህላዊ ስርዓቱ እንዲቀጥል ያደርጋል።

የብሄር ፌደራል ስቴቱ ስልጣን ምንምን ላይ ነው?

የብሄር ፌደራል ስቴቱ የሚከተሉትን ስራዎች ያከናውናል

1.የባህል ጥበቃ ስራ

በዚህ በባህል ጥበቃ ስራ ውስጥ ተጨባጭ የሆኑና ያልሆኑ ባህሎች ይጠቀሳሉ። ተጨባጭ ( tangible culture) የምንላቸው እንደ ቅርሳቅርስ ያሉ ተጨባጭ ጉዳዮችን ነው። በአንጻሩ ተጨባጭ ያልሆኑ የምንላቸው ( intangible ) ደግሞ የተለያዩ ወግ ልማዶች፣ ሙዚቃዎች፣ ስነቃሎች፣ የሰርግ የለቅሶ ወጎች ወዘተን ይመለከታል። ስለዚህ የባህል ጥበቃ ሲሰራ በነዚህ ሁለት ክፍሎች ላይ ትኩረት ይደረጋል።

2.የሰላምና እርቅ ስራ

ለሰላምና ለእርቅ ስራ የሚሆኑ ጥበቦች በየባህሉ ይገኛሉ። እነዚህን ጥበቦች አውጥተን ለሰላም ግንባታ ለማዋል ይሀ ቤት ብዙ ይጠቅመናል። የፍትህ ስርዓታችንን ለመጠበቅም ይህ በየባህሉ ውስጥ ያሉ የእርቅና የካሳ ባህሎቻችን ሊያድጉ ይገባልና ይህ ቤት ይጠቅመናል።

3.የብሄራዊ ሙዚ

የሙዚየም ስራ ከፖለቲካው መንግስት እጅ ወጥቶ በአርበኞቹ ቤት ይተዳደራል። በየብሄሩ የብሄራዊ ሙዚየም ግንባታ ኣካሂዶ ታሪካችንን ለእይታ ያቀርባል።

4.የኬር ቴከር  ስራ

የአርበኞች ቤት በሆነ ቀውጢ ሰዓት ማለትም ማእከላዊ መንግስት ቢፈርስ የኬር ቴከር ስራ ሰርቶ ስልጣን ለተመራጩ ያስረክባል።

የዜጎች የፌደራል ስቴት

የዜጎች የፌደራል ስቴት ሁለት መንግስታት ይኖሩታል። አንደኛው መንግስት የፌደራሉ መንግስት ሲሆን ሁለተኛው መንግስት የካንቶን መንግስት ነው። ኢትዮጵያ እስራ ሁለት ካንቶኖችን ልትፈጥር ትችላለች። እነዚህ ካንቶኖች ሲቋቋሙ የስበት ህጎቻቸውን በዜግነት ላይ ያደርጋሉ። ካንቶኖች የሚቋቋሙት በቡድን ስም ለቡድን ሳይሆን ለዜጎች ይሆናል። ዜጋው በመረጠው ካንቶን መኖር መብቱ ይጠበቃል። ካንቶኖችና ፌደራል መንግስቱ ወይም የጋራው ቤታችን በህገ መንግስት የስራ ክፍፍል ያደርጋሉ። የሱፕሪም ክላውዝ ስልጣን ለጋራው ቤታችን ይሰጠዋል።የፌደራል መንግስት በሴነት፣ በኮንግረስ፣ በፕሬዚደንቱ ጽህፈት ቤትና በፍ ት ህ አካሉ ይዋቀራል። ፕሬዚደንቱ ጠቅላይ ሚንስትር ይሾማሉ። በስራቸው ሚንስትሮችና ኤጀንሲዎች ይኖራሉ። ህግ የመተርጎም ስራን የሄራ ዳኛ ይረከባል።ይህ ፌደራል ስቴት ልማት፣ የውጭ ጉዳይን፣ ጦሩን፣ ኢኮኖሚውን ሁሉ ይመራል።

ሁለቱ ስቴቶች እንዴት ይተሳሰራሉ?

የብሄር ፌደራል ስቴቱና የዜጎች ፌደራል ስቴቱ የሚተሳሰሩት በሃገራዊ ኪዳኑና በሄራው ነው። ሄራው ላይ በሚቀመጥ የስራ ክፍፍል መሰረት ስራቸውን ያከናውናሉ።

4.ተግባቦታችንና ቋንቋ

አንድን ማህበረሰብ ከሚያስተሳስረው ማህበራዊ ሃብት መካከል ዋናው ቋንቋ ነው። ቋንቋ በ IEDF ውቅር መሰረት በሚከተሉት ኣቅጣጫዎች ይታያል

1.ቋንቋ የማንነት መገለጫ ነው

ብሄሮች ቋንቋቸውን የማንነታቸው መገለጫ ኣድርገው ሊያዩት ይችላሉ።

2.ቋንቋ ከማንነት መገለጫነቱ በተጨመሪ የመግባቢያ መሳሪያ ነው

3.ቋንቋ ማህበራዊ ሃብት (Social capital) ነው

 

የ  IEDF የቋንቋ ኣያያዝና ኣሰራር

      1. ብሄራዊ ቋንቋ

በIEDF መዋቅር መሰረት ብሄራዊ ቋንቋ የምንለው ሁሉንም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ነው። ሁሉም ቋንቋዎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በመሆናቸው የብሄራዊነት ደረጃ በህገ መንግስት ይጎናጸፋሉ። ዝርዝራቸው በህገ-መንግስታችን ይጻፋል።ብሄራዊ ይባላሉ።

      1. የህብረት ቋንቋ

የህብረት ቋንቋ የምንለው ደግሞ ካሉን ቋንቋዎች ኣንዱ በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች የስራ ቋንቋ ሆኖ እንዲሰራ የምናደርገው ቋንቋ ነው። ዜጎች የመነቃነቅ መብታቸው የተከበረ ሲሆን በሄዱበት ቦታ ሊገለገሉበትና ሊግባቡበት የሚችሉት የማህበር ቋንቋ ይኖረናል።

      1. ኦፊሺያል ቋንቋ

በIEDF መዋቅር መሰረት ሁሉም ቋንቋዎች በታችኛው የስልጣን ርከን ላይ ኦፊሺያል ይሆናሉ። ይህ ማለት በታችኛው የስልጣን ርከን ላይ ዜጎች ወይ በህብረቱ ቋንቋ ወይ በአካባቢው ቋንቋ ይገለገላሉ ስራውም በነዚህ ቋንቋዎች ይካሄዳል ማለት ነው።

      1. ዲፋክቶ ቋንቋ

እንግሊዘኛ የሃገራችን ዲፋክቶ የስራ ቋንቋ ሆኖ እንዲሰራ ማድረግ

      1. የቋንቋ አካዳሚዎችን ማስፋፋት

ሌላው ጉዳይ የቋንቋ ኣካዳሚዎችን በማስፋፋት ዜጎች ባይልንጉዋል እንዲሆኑ መስራት ነው።

 

የ IEDF ዓላማዎች

 

  IEDF የሚከተሉትን ዓላማዎች ኣንግቦ የተነሳ ድርጅት ነው።

 1. ከፍ ሲል እንደተገለጸው ይህ የ IEDF ኣሳብ ለብሄራዊ መግባቢያነት እንዲውልና ሽግግራችን የተሻለ እንዲሆን ማድረግ

 1. የፌደራሊዝም ጽንሰ ሃስብን ማስፋፋትና በተለይም ፌደራሊዝሙን ኢትዮጵያዊ ማድረግ

 1. ይህንን የ IEDF መዋቅር ለማዳበርና ለማስተማር የሚችል የጥናት ተቋም መፍጠርና በዚህ መዋቅር ዙሪያ ምርምሮችን እየሰሩ ስርዓቱን ማዳበር የጠፉ ጠቃሚ ባህሎችንና እሴቶችን መመለስ

IEDF ሃይማኖትን እንዴት ያየዋል?

ሃይማኖት ከዚህኛው ዓለም በላይ ስለሚመጣው ዓለም የሚጨነቅ ነው። ይህ ስብስብ ዓለማቀፋዊ ባህርይም ኣለው። ዲኖሚኔሽኖች ያድጋሉ ይጠፋሉ። ነገር ግን ለመንግስት ትልቅ ማህበራዊ ሃብት ናቸው። ስለዚህ እነዚህን ተቋማት ሁሉ መንግስት የመንከባከብ ከጥቃት የመጠበቅ ሃላፊነት ያለበት ሲሆን ነገር ግን መንግስትና ሃይማኖት ተለያይተው ይኖራሉ። መንግስት የሃይማኖት ተቋማትን ኣያደረጅም ኣያፈርስም። ነገር ግን ይጠብቃቸዋል በህጉ መሰረት ይደግፋቸዋል::

ሃይማኖት ነክ ባህሎች Semi culture እንዴትይታያሉ?

በIEDF እይታ ሃይማኖት ነክ ባህሎች በብሄር ፌደራል ስርዓቱ ውስጥ ታቅፈው እንክብካቤ የሚደረግላቸው ይሆናል። ወደ ሃይማኖት ካደሉ ከዚህ መዋቅር እየወጡ የራሳቸውን ሃይማኖት ማራመድ ይችላሉ።

የ IEDF እሴቶች ምን ምን ናቸው?

  • ሃገራዊ ኪዳን Covenant

  • ብዝሃነት pluralism

  • መግባባት Consensus

  • መርህ principle

ይህንን የ IEDF የመንግስት መዋቅር በስእላዊ መንገድ ማሳየት ይቻላል ወይ?

ይቻላል! የሚከተለው የመንግስት መዋቅር የIEDFን ኣሳብ የሚገልጽ መዋቅር

ይህንን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ  IEDF house 2019    ወይም መግቢያ ላይ ያለውን ቤት ይመልከቱ

 

 

ማጠቃለያ

ይህ ዶክመንት የተዘጋጀው IEDFን ለማስተዋወቅና ዝንባሌን ለመሳብ ነው። IEDF ለሃገራችን ሽግግር ግሩም ኣስታራቂ ሃሳብ ነው ብለን እናምናለን። ይህንን ኣሳብ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማህበራት ምሁራን እንዲቀበሉት (endorse እንዲያደርጉት) ጥሪ እናደርጋለን። በአጠቃላይ አስታራቂ ወይም አግባቢ ኣሳብ የምንለው ከፍ ሲል የሰራነውን መዋቅር ነው። ይህንን መዋቅር ለጋራ መግባቢያ ብናደርገውና ወደ መድብለ ፓርቲ ስርዓት ብንሻገር ወደ ዴሞክራሲ የምናደርገው ግስጋሴ ይፈጥናል ሰላምና መረጋጋትን አምጥተን ኢትዮጵያን እናበለጽጋለን የሚል ጽኑ እምነት ኣለን።

 

                              Info@ethiofederalism.org

                            እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ !

 

ከ IEDF  ጋር በመተባበር ለመስራት ፍላጎት ካሎት ከታች ያለውን ፎርም በመሙላት ያስታውቁን!

Please enter your email, so we can follow up with you.